በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና ተሰጠ፡፡

የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ዓመታት በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት HCP (Himalan Cataract Project ) ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመፈራረም ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል፡፡
በመሆኑም በስምምነቱ መሠረት ለ2ኛ ዙር የድርጅቱ ተወካይ አቶ ሀገሩ ከበደ በተገኙበት ከ17/03/2016-21/03/2016 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ነፃ የአይን ሞራ ግርዶሾ ቀዶ ጥገና በሆስፒታሉ እየተሰጠ ይገኛል፡፡ የቀዶ ጥገና ዘመቻ ሥራዉን በሚመለከት ማብራሪያ የሰጡት በሆስፒታሉ የዓይን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር አያኖ ባሳዝን ድርጅቱ "Cure blindness" የሚል መሪ ቃል ይዞ የሚሰራ መሆኑን በመግለጽ የዓይን ሞራ ግርዶሽ በአመዛኙ ሰዎች እድሜያቸዉ  ከ55 በላይ ሲሆን የሚከሰት መሆኑን እና በተጨማርም በዓይን ላይ በሚደርስ አደጋ እና በሌሎች የዓይን በሽታዎች እንዲሁም አብሮ በመወለድ የሚመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለ2ኛ ዙር የዓይን ሞራ ቀዶ ጥገና ለመስጠት በዕቅድ የተያዘው 400 ሰዉ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አያኖ ለእነዚህ ታካሚዎችም የህክምናዉ ሙሉ ወጪ በድርጅቱ ድጋፍ የተሸፈነ መሆኑን አስረድቷል፡፡ 
የሆስፒታሉ ቺፍ ክሊኒካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ታሪኩ ጋሪ በበኩላቸዉ ሆስፒሉ ከተለያዩ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጤናዉ ዘርፍ የተለያዩ ሥራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ አቅዶ እየሠራ መሆኑን በመጠቆም ይህ በዓይን ሞራ ግርዶሽ ላይ እየተሠራ ያለዉ ሥራም ከተደረጉት ስምምነቶች መካከል አንዱ መሆኑን እና ከዞኑ አልፎም ለጎረቤት ዞኖችና ወረዳዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግሯል፡፡