በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ነፃ የአይን ሞራ ግርዶሽ የቀዶ ህክምና ዘመቻ ሥራ ከእቅድ በላይ በመፈፀም ተጠናቀቀ።

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ሐምሌ 11/2017 ዓ.ም (BHU)

በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ከሐምሌ 7-11/2017 ዓ.ም ለተከታታይ አምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ከክፍያ ነፃ የአይን ሞራ ግርዶሽ የቀዶ ህክምና ዘመቻ ሥራ ለ500 ግለሰቦች አግልግሎቱን ለመስጠት ታቅዶ ለ523 ሰዎች ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት በመስጠትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ህክምናውን ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ ለመጡ ነገር ግን በተደረገው ምርምራ የአይን ሞራ ግርዶሽ ጋር ያልተገናኘ ለ1200 ሰዎች ጭምር ነፃ ምርምራና አስፈላጊውን መድሃኒት በመስጠት በስኬት ስለ መጠናቀቁ ተገልፆዋል።

የዘመቻ ሥራው በስኬት መጠናቀቅን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በም/ፕሬዝዳንት ማዕረግ የጤና ኢንሲቲትዩት ቺፍ ኤክስኪዩቲቨ ዳይሬክተር ዶ/ር ሳፋይ ኤሌማ ዩኒቨርሲው በአይን ህክምና ዙሪያ ከCure blindness Project ጋር ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ላለፉት ሦስት ተከታታይ አመታት ከ4500 በላይ በአይን ሞራ ግርዶሽ ተጠቂ ለሆኑ ግለሰቦች ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠት መቻሉን ያስረዱ ሲሆን በዘንድሮ ዓመትም ከCure blindness Project በጋራ እየሠራባቸው ካሉ ሃያ ስድስት አጋር ድርጅቶች መካከል የህክምና ጥራትን ለመጨመር በሚል በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ይደረጋሉ ተብለው እንደ ሀገር ከተመረጡ አምስት ሆስፒታሎች መካከል አንዱ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል መሆኑን ጠቅሰዋል።

አያይዘውም ዶ/ር ሳፋይ የተለያዩ ችግሮች ሳይገድባቸው በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በማቋረጥ መጥተው ይህን አገልግሎት የሰጡት ህክምና ባለሙያችን ከዩኒቨርሲቲው በላይ የአይን ብርሃናቸውን መልሰው ያገኙ ግለሰቦች ለዘላለም የሚያስታውሷቸው ስለመሆኑ ገልፀው በቀጣይም ከህክምና ቡድኑ ጋር የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር ተመሳሳይ ሥራዎችን ለመስራት ዩኒቨርሲቲው ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀውላቸዋል።

በመጨረሻም ዶ/ር ሳፋይ ባስተላለፉት መልዕክት በማስተማሪያ ሆስፒታሉ በኩልም በዚህ ታላቅ ተግባር ላይ ሙያዊ ግደታቸውን ለተወጡት ሁሉ ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን በተለየ መልኩ የማስተማሪያ ሆስፒታሉ የአይን ህክምና ስፔሻሊስቲና የዓይን ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶ/ር አያኖ ቢያሳዚን ለሥራው ስኬት ያሳዩት ቁርጠኝነት ሌሎች አርኦያ የሚሆን ነው ሲሉ አስረድቷል።

የሆስፒታሉ መድካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሀሰን በበኩላቸው በዘንድሮ አመት በተደረገው ዘመቻ ሥራም ከዕቅድ በላይ በመፈፀም የመጠናቀቁ ምስጥር አስቀድሞ የተለያዩ ችግሮችን በመቋቋም ወደ ተለያዩ አጎራባች ዞኖች ጭምር በመሄድ ቅስቀሳ መደረጉና የህክምና ቡድኑ የመጡበትን አላማ ተገንዝበው ለወገናቸው ባሳዩት ቁርጠኛ ተግባር የተገኘ ስኬት ስለ መሆኑ ያስረዱ ሲሄን የተገኘው ውጤት አሁንም በተለያዩ ምክንያቶች የአይን ብርሃናቸውን አጥተው በየቤቱ ተቀምጠው ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች የተዳረጉ በርካታ ወገኖች እንዳሉ አመላካች በመሆኑ በቀጣይ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ ገልፀዋል።

በዘመቻ ሥራው ላይ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታሉን የህክምና ባለሙያዎች እና ሌሎች በበጎ አድራጎት መልክ የተሳተፉ የህክምና ተማሪዎችን ሳይጨምር ከሌሎች ሆስፒታሎች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ሰብ ስፔሻሊስትና ስፔሻልስቲ ዶክተሮችን ጨምሮ 20 አባላት የተሳተፉበት ስለ መሆኑ ተገልፆዋል።