በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን ለመዉጫ ፈተና ከማዘጋጀት አኳያ ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር የፓናል ዉይይት ተካሄደ፡፡

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ህዳር 21/2017 (BHU)
ትምህርት ሚኒስቴር በሀገር ደረጃ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በወሳኝ ደረጃ ካስቀመጣቸዉ የሪፎርም ሥራዎች መካከል ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚመረቁ ተማሪዎች የሚሰጥ የመዉጫ ፈተና አንዱ ነዉ፡፡
በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲም እተማሩ ያሉ ተማሪዎች የመዉጫ ፈተናዉን በብቃት ማለፍ እንዲችሉ እስካአሁን በነበሩት መዉጫ ፈተና አፈፃፀሞች፤እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በሚመለከትና ለቀጣዩ መዉጫ ፈተና ተማሪዎችን ከማዘጋጀት አንፃር የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማን ጨምሮ አካዳሚክ ምርምር፤ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህብረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገበየሁ አሻግረ፤ ዲኖች የኢንስቲትዩትና የትምህርት ቤት ዳይሬክተሮች፤ መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት የጋራ ዉይይት ተደርጓል፡፡
ዶ/ር ብርሃኑ በዉይይቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከዋነኛ ተልዕኮዎቹ መካከል ጥራትና ብቃት ያላቸዉ ተማሪዎችን ማፍራት አንዱ መሆኑን በመጥቀስ በዩኒቨርሲቲዉም ትምህርታቸዉን እየተከታተሉ ያሉ ተመራቂ ተማሪዎች በመጨረሻ ላይ በሀገር ደረጃ ወጥና በተመሳሳይ ሰዓት በሚሰጥ መዉጫ ፈተና ላይ ማለፍ እንዲችሉ ከወዲሁ ተከታታይና የተቀናጀ ሥራ በመሥራት በዩኒቨርሲቲዉ የተማሪዎችን መዉጫ ፈተና የማለፍ ምጣኔ ከፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አያይዘዉም ፕሬዝዳንቱ ያስተማርናቸዉ ተማሪዎች መዉጫ ፈተናዉን እንዲያልፉ ማድረጉ ጥቅሙ ለተማሪዉ ብቻ ሳይሆን በመማር ማስተማሩ ሂደት አብሮ ለቆዩ መምህራንና ድጋፍ ሰጭ ሠራተኞች እንዲሁም ከምንም በላይ የነገዉን ሀገር ተረካቢ ዜጋ ዝግጁ ከማድረግ አንፃርም ጥቅሙ የጎላ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በዉይይቱ ላይ የተገኙ የኮሌጅ ዲኖችና ዳይሬክተሮችም በየተራ የነበረዉን አፈፃፀምና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን እንዲሁም ለቀጣይ ተማሪን ከማዘጋጀት አንፃር የተቀየሱ ስልቶችን በማቅረብ ዉይይት ያደረጉ ሲሆን በዉይይታቸዉም በተማሪዎች መካከል የእርስ በርስ የመደጋገፍ ስልት በመቀየስ፤በየኮሌጁ መምህራን ከመደበኛዉ ትምህርት ሰዓት በተጨማሪ ቲቶሪያል ትምህርት እንዲሰጡና አፈፀፀሙንም ተከታታይነት ባለዉ መልኩ በመገምገም ተማሪዎቹን ከወዲሁ ማዘጋጀቱ አስፈላጊ መሆኑ የጋራ ግንዛቤ ተይዞ ዉይይቱ ተጠናቋል፡፡