በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የ2017 ዓ.ም የ1ኛ ሩብ ዓመት የሥራ ክንዉን ሪፖርት ቀርቦ ዉይይት ተካሄደ፡፡
ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም
ዩኒቨርሲቲዉ በ2017 ዓ.ም በአንደኛ ሩብ ዓመት ለማከናወን ያቀደዉን ዕቅድ ከመተግበር አንጻር የሥራ ክንዉኑ በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችና የየዘርፉ ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል፡፡
ሪፖርቱ የቀረበዉ በዩኒቨርሲቲዉ የዕቅድ በጀትና ክትትል ሥራ አስፈፃሚ በሆኑት በአቶ መሰለ አለማየሁ ሲሆን በበጀት ዓመቱ በ1ኛ ሩብ ዓመት በሦስት ወራት ዉስጥ የመማር ማስተማሩን ሥራ ጨምሮ ሌሎችንም ተግባራት በየግቡና በተቀመጠለት ስትራቴጅክ ዓላማ መሠረት በማቀናጀት በዝርዝር አቅርበዉ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በቀረበዉ ሪፖርት መሠረት በጠንካራ ጎን ከተመዘገቡት መካከል ከመማር ማስተማሩ ጋር ተያይዞ ለ2017 ዓ.ም የቅድመ ዝግጅት ሥራን በተመለከተ ከተለያዩ ግብዓቶች ዝግጅት ጋር ተያይዞ የመማርያ ክፍሎች እድሳት፤የመኝታና መመገቢያ ካፍቴሪያዎች አካባቢ ጨምሮ አስፈላጊዉ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን ከበተ-መጽሐፍትና ከተለያዩ ላብራቶሪዎች አደረጃጀት ጋርም ተያይዞ በየዘርፉ መደራጀታቸዉ በሪፖርቱ ላይ በበጎ ጎን ከተገመገሙት መካከል ይገኛሉ፡፡
በሌላ መልኩ ስድስት የተለያዩ የጥናትና የምርምር ስራዎች በመምህራን የተሠሩ ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ በሆኑ ጆርናሎች ላይ መታተማቸዉና ወደ ሃያ የሚጠጉ ደግሞ ሌሎች የምርምር ፕሮፖዛሎች ወደ ሥራ ለማስገባት አስፈላጊዉ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁንም ዳይሬክቶሬቱ ገልጾዋል፡፡
በመጨረሻም በሪፖርቱ ላይ አስፈላጊዉ ዉይይት ከተደረገ በኃላ በዉስንነት የተመዘገቡ ነጥቦችን በሚመለከት የየዘርፉ ኃላፊዎች በቀጣይ የክንዉን ወራት ዉስጥ የዕቅዱ አካል በማድረግ የተሻለ ዉጤት ማስመዝገብ እንዳለባቸዉ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማ አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡