የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስቲር ዴኤታና የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰቢሳቢ የሆኑት ዶ/ር ኬይረዲን ተዘራን ጨምሮ የቦርድ አባላት በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አስመልክተው የመስክ ምልከታ አደረጉ፡፡
Posted by admin on Tuesday, 17 December 2024
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ታኅሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ.ም (BHU)
ቦርዱ ያደረገዉ የመስክ ምልከታ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲዉ ከሦስት ወራት በፊት ያለበትን የሥራ አፈፃፀም ደረጃ ከገመገመ በኃላ በቀጣይ ሦስት ወራት ዉስጥ መስተካከል አለባቸዉ ብሎ አቅጣጫ ባስቀመጠው መሠረት የተከናወኑ ሥራዎችን ታሳቢ ያደረገ የመስክ ምልከታ እንደሆነ በምልከታው ወቅት ተገልጾዋል፡፡
በመስክ ምልከታዉ ሂደት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስቲር ዴኤታና የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰቢሳቢ ዶ/ር ኬይረዲን ተዘራን ጨምሮ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማ እንዱሁም ም/ ፕሬዝዳንቶች፤የዩኒቨርሲቲዉ ካዉንስል አባላት፤የቡሌ ሆራ ከተማ ከንቲባና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ጭምር በመስክ ምልከታዉ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በአጠቃላይ የመስክ ምልከታዉ ከተማሪዎች መሠረታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያያዥነት ባላቸዉ ጉዳዮች፤የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል እና በዩኒቨርሲቲዉ እየተከናወነ ያለዉ የግብርና ሥራዎች የመስክ ምልከታ ከተደረገባቸዉ መካከል ይገኛሉ፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስቲር ዴኤታና የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰቢሳቢ የሆኑት ዶ/ር ኬይረዲን ተዘራ የመስክ ምልከታዉን እና አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲዉን ሥራ አፈፃፀም በማስመልከት ከካዉንስል አባላቱ ጋር ባደረጉት ዉይይት ዩኒቨርሲቲዉ ቀደም ሲል በመስክ ምልከታ ወቅት እንደ ጉድለት ታይቶ የነበሩትን በማሻሻል በአሁኑ ሰዓት በጥሩ ደረጃ ላይ ያለ ስለመሆኑ ተናግሯል፡፡
አያይዘዉም የሰላም ሚኒስተር ዴኤታና የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰቢሳቢ ዶ/ር ኬይረዲን ዩኒቨርሲቲዉ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተለየ መልኩ የመልማት ፀጋ እና እምቅ አቅም ያለዉ መሆኑንና፤በሀገር በቀል ዕዉቀት ላይ ጭምር እየሠራ ያለዉን ሥራ በማጠናከር የጉጂን ባህል ይዞ ከጎረበት ሀገሮች ጋር ጭምር ለህዝቦች ሠላምና አንድነት ማጠናከርና መሥራት የሚችል ዩኒቨርሲቲ መሆኑ እና በአሁኑ ሰዓትም ከሦስተኛ ትዉልድ ዩኒቨርሲቲዎች በተሻለ ደረጃ ላይ ያለ ስለ መሆኑ አንስቷል፡፡
በተጨማሪም ለዩኒቨርሲቲዎች ስኬታማነት የካዉንስል አባላት ሚና በጣም ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት የቦርዱ ሰብሳቢ ሥራዎችን በህብረትና በመደጋገፍ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን፤ቅድሚያ በሚሰጡ ጉዳዮች ዙሪያ በመነጋገር ቅደም ተከተል በማስያዝ መፈፀምና አፈፃፀሙን ተከታታይነት ባለዉ መልኩ መገምገሙ አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል፡፡
በመጨረሻም የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል አሁን ካለበት ደረጃ አንፃር በርካታ ማሻሻዎች የሚያስፈልጉት በመሆኑ በቅርብ ጊዜ ቡድን ተዋቅሮ የሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ ተወስዶ ደረጃዉን የጠበቀ ሆስፒታል እንዲሆን እንደሚደረግ አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይቱ ተጠናቋል።