ለቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የካዉንስል አባላት ፣ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በእቅድ እና ሪፖርት ዝግጅት እንዲሁም አተገባበር ዙርያ ስልጠና ተሰጠ

ስልጠናው የተሰጠው በቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ጫላ ዋታ ሲሆኑ፤ የእቅድ ዝግጅት ሂደት፣ የእቅድ መነሻ፣ የእቅድ አላማና ሰነድ ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዉበታል።
ተቋሙ ከመደበኛ እቅድ በተጨማሪም በልዩ እቅድ ታግዞ በርካታ ለዉጦችን ማምጣት እንደቻለ የገለጹት ፕሬዘዳንቱ በእቅድ ታግዞ መስራት ተቋማዊ እና ሀገራዊ ለውጥ ከማምጣቱ በተጨማሪ የሕዝብ ተጠቃሚነትን ያረጋግጣል ብለዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጫላ ዋታ ከሀገሪቱ የ10 አመት መሪ እቅድና ፍኖተ ብልጽግና ጋር አያይዘው የተቋሙን ተደራሽ ግቦችና ስትራቴጂካዊ ተግባራትን በሰፊው አብራርተዋል ።
በዕቅድ ታግዞና የበጀት መርህን ጠብቆ በትጋት መስራት የሀብት ብክነትን ለመቀነስ፣ የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ ፣ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የተቋሙን እሴቶች እውን ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ፕሬዚዳንቱ በአጽንኦት አንስተዋል።
በስልጠናው የ2013 በጀት አመት አፈፃፀምና የ2014 በጀት አመት አንደኛ ሩብ አመት ግምገማም ተብራርቷል ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተቋሙ የ2014 በጀት አመት እቅድ እና አተገባበር፣ ግብና ስትራቴጂካዊ አላማዎች በስፋት ስልጠናዊ ዉይይት ተደርጎባቸዋል።
የተቋሙን አቅምና ብቃት ለማሳደግ ፣ ሀገርንና ወገንን የሚወዱና የሚያከብሩ ምሩቃን እንዲፈጠሩ ለማስቻል እንዲሁም የትምህርት ጥራትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እቅድን ከበጀት ጋር በማስተሳሰር ሀላፊነትና ተጠያቂነት በተሞላበት መልኩ መስራት የሁሉም ሰራተኞች ሀላፊነት ስለመሆኑም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል ።
አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታም ተቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በማስታወስ "የሀገርና ሕዝብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ተቋማዊ እና ግለሰባዊ ዝግጁነት አስፈላጊ ነውም " ብለዋል ፕሬዘዳንቱ ።
በስልጠናው በቀረቡት ሃሳቦች ላይም ጥልቅ ውይይት ተደርጎባቸዋል ።
ለላቀ ለዉጥ እንተጋለን !!!
ሕዳር 2014 ዓ.ም
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ