በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ዘርፍ የ3ኛ ሩብ እና የ9 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ
የዘርፉ ያለፉት ዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እያንዳንዱ የሥራ ክፍል ኃላፊ ሪፖርቱን በማቅረብ የጋራ ግምገማ ተካሂዶባቸዋል። የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማው ትምህርት ሚኒስቴር ያወረደውን ቁልፍ ተግባራት መነሻ በማድረግ በመማር ማስተማር፣በምርምር እና በማህብረሰብ አገልግሎት በኩል የተከናወኑ ተግባራት ላይ ትኩረት ተደርጎ የሪፖርት ግምገማው ተካሂዷል። ከመማር ማስተማር አኳያ ተመራቂ ተማሪዎች በየ ኮሌጁ የመውጫ ፈተና የማለፍ ምጣኔ፣የማቋረጥና የመመረቅ ምጣኔዎች ከተቀመጠው ስታንዳርድ አንፃር ያለበት ሁኔታ፣ተማሪዎችን ለመውጫ ፈተና ከማብቃት አኳያ የተሰጡ ሞዴል ፈተናዎች፣በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች የመምህራንን አቅም ለማጎልበት የሚወርዱ የተለያዩ ሥልጠናዎች አፈፃፀምና በቀጣይ ወረቀት አልባ የመማር ማስተማር ሂደትን ለመከተል የእያንዳንዱ ኮሌጅ እያደረገ ያለው ጥረት በተጨባጭ ቀርቦ ተገምግሟል። ጭብጥ ተኮር የምርምር ሥራዎች ከዕቅዱ አንፃር በሦስተኛው ሩብ ዓመት የተደረሰበትና በማህብረሰብ አገልግሎት በኩልም ኮሌጆች በተቀናጀ ሁኔታ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት እያደረጉ ያሉበት ጥረትም ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል። በሪፖርት ግምገማው ወቅት በውስንነት ከተገመገሙት መካከል የትምህርት ፕሮግራሞች ኦዲትና ከእውቅና አሰጣጥ ጋር ተያይዞ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ኮሌጆች መሄድ ባለባቸው ልክ እየሄዱ ባለመሆኑ በተቋቋሙት ኮሚቴዎች አማካይነት በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ መመሪያ የተሰጠ ሲሆን ሪፖርትን በጊዜ አጠናቅሮ ከመላክ አንፃር የሚታዩ ክፍተቶች እንዲሻሻሉም የጽ/ቤቱ ኃላፊ ዶ/ር ተስፋዬ አሳስቧል።



