በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች ሲካሄድ የቆየዉ ብሔራዊ የበጎ አድራጎት ሥራ ተጠናቀቀ፡፡

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ፣ ነሐሴ 18፣ 2016 ዓ/ም (BHU)

በሠላም ሚኒስቴርና በትምህርት ሚኒስቴር የበላይ አስተባባሪነት ላለፉት 25 ቀናት በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አማካኝነት በቡሌ ሆራ ከተማ ሲከናወን የቆየዉ ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ተጠናቆ በዛሬዉ ዕለት የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማን ጨምሮ የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር መታሰቢያ አዱላና ሌሎችም በተገኙበት የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ተከናዉኗል፡፡

በመዝጊያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማ በክረምት ቤተሰብ ጋር መሄድ ሲገባቸዉ ማህብረሰቡን እናገለግላለን ብሎ በመቅረት ይህን ታሪክ የማይረሳዉን ሥራ ላከናወኑ ተማሪዎች የላቀ ምስጋና አቅርቧል፡፡

አያይዘዉም ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ጠንካራና አንድነቷ የተጠበቀ ሀገር ለማስቀጠል ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ በጣም አጋዥ መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይም ተማሪዎች ወደ አካባቢያቸዉ ሲመለሱ በቀለምና በተግባር በቀሰሙት ዕዉቀት መሠረት ማህብረሰቡን እንዲያገለግሉ ያሳሰቡ ሲሆን ዩኒቨርሲቲዉ በቀጣይም በተደራጀ መልኩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ተናግሯል፡፡

በሌላ መልኩ የበጎ ፈቃድ ሥራ አስተባባሪዉ ተማሪ ጎዳና በበጎ ፈቃድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ተማሪዎች በ7 ቡድን ተከፋፍለዉ በቡሌ ሆራ ከተማ በተለያዩ ሥራ ዘርፎች ማህብረሰቡን ሲያገለግሉ የቆዩ መሆናቸዉን በመግለጽ ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋናዉን አቅርቧል፡፡

በመጨረሻም በእያንዳንዱ ቡንድን የተከናወኑ ሥራዎች በአስተባባሪዎቻቸዉ አማካኝነት ገለፃ ተደርጎ የፕሮግራሙ ማሳረጊያ ሆኗል፡፡