በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ዙሪያ ወርክሾፕ ተካሄደ፡፡
ጥቅምት 22/2017 ዓ.ም
“Transformative Research through Gender lens: Implications for Science, Innovation, and Technology`` በሚል ርዕስ በዩኒቨርሲቲዉ ያሉ ሴት መምህራን የጥናትና ምርምራ ተሳትፎ ማሳደግን ዓላማ ያደረገ የጥናትና ምርምር ወርክሾፕ የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
ወርክሾፑ የዩኒቨርሲቲዉ የምርምር፤ሕትመት፤ሥነ-ምግባርና ሥርፀት ሥራ አስፈፃሚ አስተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን የክፍሉ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አብነት በቀለ ዩኒቨርሲቲዉ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያለዉን የጥናትና ምርምር ጉዞ ሂደት ገለፃ በማድረግ የሴት መምህራን የጥናትና ምርምር ተሳትፎም ከነበረበት 2.8% ወደ 5.6% ከፍ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸዉን ገልጾዋል፡፡
በጥናትና ምርምሩ ወርክሾፕ ላይ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማ ተገኝተዉ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን እየተካሄደ ያለዉ ወርክሾፕ በጣም አስፈላጊና ጊዜዉን የጠበቀ መሆኑን በመግለጽ ሴት መምህራን በጥናትና ምርምሩ ዙሪያ አቅማቸዉን በማጎልበት የማህብረሰቡን ችግር ከመፍታት አኳያ አይነተኛ ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲዉ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
በሌላ መልኩ በዕለቱ የክብር እንግዳ በመሆን የተጋበዙት ዶ/ር አቻምየለሽ ገ/ፃድቅ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በርዕሰ ጉዳዩ ዙሪያ የዳሰሳ ዉጤት በማቅረብ የተካሄደዉ ወርክሾፕም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ዶ/ር መታሰቢያ አዱላ “Gender equality in research and innovation:a contemporary challenges at Bule Hora University`` በሚል ርዕስ ያቀረቡ ሲሆን እንዲሁም ዕጩ ዶ/ር ብርሃነ አጥናፉም “Experience of Women in Ethiopian Higher Education`` በሚል ርዕስ የምርምር ሥራዎቻቸዉን ካቀረቡት መካከል ይገኛሉ፡፡