በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የ”GAT”ፈተናና ምዝናን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።

ሀምሌ 20/2016 ዓ/ም
የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠዉ አቅጣጫ መሰረት ክዚህ በኋላ ትምህርታቸዉን በ2ኛና 3ኛ ዲግሪ መቀጠል ለሚፈልጉ መምህራን፣ ሌሎች የመንግስት ሰራተኞችና ግልሰቦች ማሟላት ከሚገባቸዉ መስፈርቶች አንዱ የሆነዉ የGAT(Graduation Admission Test) ፈተናና ምዘናን ወስዶ ማለፍ መቻል ነዉ።
በስልጠናዉ ላይ በመገኘት ስልጠናዉን በንግግርና ሃሳብ በመስጠት ያስጀመሩት የዩኒቨርሲቲዉ የአካዳሚክ፣ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ትንሳኤ ታምራት ናቸዉ። በንግግራቸዉ ካነሷቸዉ ሃሳብ አንዱ የጋት ፈተናን ወስዶ ማለፍ ከተቀመጠዉ አቅጣጫ ዋነኛዉ መስፈርት ሲሆን፣ እያንዳንዱ አመልካች ተማሪ ይሄንን ተገንዝቦ ስልጠናዉን በተኩረትና በመረጋጋት መዉሰድ እንዳለበት አስምረዉበት አሳስበዋል።
ከ1ኛ ዲግሪ በላይ ባሉት የትምህርት ደረጃ ትምህርታቸዉን ለመቀጠል ይህን የመግቢያ ፈተና መዉሰድ ግዴታ ከሆነ፣ ለትምህርቱ የሚያመልክቱ አመልካቾች የGAT ፈተናን ይዘትና አጠቃላይ አዘገጃጀት ማወቅ አስፈላጊና መሰረታዊ ጉዳይ ስለሆነ፣ ይሄንኑ በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀዉን ስልጠና መዉሰድ አስፈላጊ መሆኑን ስለታመነበት ስልጠናዉ እንዲሰጥ ተደርጓል።
በዚሁ መሰረት ስልጠናዉን ለመስጠት ይመጥናሉ ተብለዉ የታመነባቸዉ የዩኒቨርሲቲዉ መምህራን በTOT ስልጠና ላይ እንዲሳተፉ ተልከዉ የነበሩ መምህራን ስልጠናዉን እንዲሰጡ ተደርጓል።ስልጠናዉ ትኩረት ያደረገባቸዉ የትምህርት አይነቶች፣የእንግሊዘኛ ቋንቋ፣ሂሳብ የፍልስፍናና የስታስቲክስ ትምህርቶች ናቸዉ።
እንደተቋሙ ስልጠናዉን ያስተባበሩትና ለዝግጅቱ ሃላፊነቱን ወስደዉ ለተግባራዊነቱ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ የዩኒቨርሲቲዉ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ዳይሬቶሬትና የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬቶች ሲሆኑ በአጠቃላይ ስልጠናዉ የተሰጣቸዉ አካላት፣የዩኒቨርሲቲዉ መምህራን፣የአስተዳደር ሰራተኞች፣የአካባቢዉ የመንግስት ሰራተኞችና የትምህርት ፍላጎት ያላቸዉ ግለሰቦች ናቸዉ። በጠቅላላ ስልጠናዉን የወሰዱ ስልጣኞች ብዛት ወንድ 171 ሴቶች 20 በድምሩ 191 ይሆናሉ።