በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የ2016 ዓ.ም የ4ኛ ሩብ ዓመትና የ12 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድን በተመለከተ ዉይይት ተካሄደ፡፡

ነሃሴ 01/2016 ዓ.ም

ዩኒቨርሲቲዉ በ2016 ዓ.ም ለማከናወን ያቀደዉን ዕቅድ ከመተግበር አንጻር በበጀት ዓመቱ አራተኛ ሩብ ዓመትን ጨምሮ የዓመቱ የሥራ ክንዉን በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችና የየዘርፉ ኃላፊዎች በተገኙበት ተገምግሟል፡፡

ሪፖርቱ የቀረበዉ በዩኒቨርሲቲዉ የእስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ በአቶ መሰለ አለማየሁ ሲሆን በበጀት ዓመቱ በ4ኛ ሩብ ዓመት እና በ12 ወራት ዉስጥ የመማር ማስተማሩን ሥራ ጨምሮ ሌሎችንም ተግባራት በየግቡና በተቀመጠለት ስትራቴጅክ ዓላማ መሠረት በጠንካራ ጎን የተመዘገቡ እንዱሁም ዉስንነት የታዩባቸዉን ጉዳዮችና በትግበራ ወቅት ተግዳሮት የገጠማቸዉ እንደ ፋይናንሽያል ሪፖርት ጋር በማቀናጀት በዝርዝር አቀርበዉ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በቀረበዉ ሪፖርት መሠረት በጠንካራ ጎን የተመዘገቡ ከመማር ማስተማሩና ተማሪዎችን ለመዉጫ ፈተና ከማዘጋጀት አኳያ የተሠሩ ስራዎችና የተመዘገቡ ዉጤቶች ከ2015 ዓ.ም የተሻለ ሆኖ ተገኚቷል።በዚሁ መሰረት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን በተመለከተ መንግስት ያወረደዉን መመሪያ ተከትሎ የግዥ ሂደቶች በኤልክትሮኒክስ ግዥ መፈፀማቸዉ፤በሀገር በቀል ዕወቀት ላይ በተሰራዉ አመርቂ የምርምር ስራ የተቋሙ ጆርናል ዕዉቅና ማግኘቱ፤አዲሱ የሠራተኞች የሥራ ምደባን በተመለከተ ከቡድን መሪ በላይ ያሉ መዋቅሮች ላይ ምደባ መጠናቀቁና የባለሙያዎች ምደባም በመጠናቀቅ ላይ መገኘቱ፤በተለያዩ ኮሌጆችና ሥራ አስፈፃሚዎች አማካይነት የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች መሰጠታቸዉ፤ከማስተማሪያ ሆስፒታሉ ጋርም ተያይዞ በበጀት ዓመቱ ከ145,280 በላይ ለሆኑ ህሙማን የህክምና አገልግሎት መሰጠቱና ሂማሊያን ካታራክት ከተባለ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ለበርካታ ሰዎች ነፃ የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ጥገና መሰጠቱ ጎልቶ ከወጡ ጠንካራ አፈፃፀሞች መካከል ናቸዉ።

በተጨማሪም በዉስንነት የተመዘገቡ ነጥቦችን በሚመለከት የየዘርፉ ኃላፊዎች የ2017 ዓ.ም ዕቅድ አካል በማድረግ የተሻለ ዉጤት ማስመዝገብ እንዳለባቸዉ የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማ ጥብቅ የስራ መመሪያና አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የ2017 ዓ.ም የተቋሙን የስራ ዕቅድ በተመለከተ ለተሳታፊዎች ቀርቦ ዉይይት የተደረገ ሲሆን ወደ ተግባር ከመቀየር አኳያ የሚመለከታቸዉ አካላት ተግተዉ እንዲሠሩና የሥራ ክንዉን ሪፖርትም ወቅቱን ጠብቆ ለሚመለከተዉ የሥራ ክፍል እንዲደርስ የሥራ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡