የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት አደረገ
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ፣ ነሐሴ 15፣ 2016 ዓ/ም (BHU)
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታልና የጤና ኢንስቲትዩቱ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ሳፋይ ኤሌማ ከወትሮው በተለየ መልኩ ለዉይይት የተጠሩት ሰራተኞች በመገኘታቸው ደስታቸውን በመግለጽና ታዳሚዎቹን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የእለቱን አጀንዳ በማስተዋወቅ ዉይይቱን ያስጀመሩ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ሆስፒታሉ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት ለማድረግ ቢያስብም በወቅቱ በቂ ዉይይት ማድረግ አልተቻለም።ይሁን እንጂ ከረዥም ጊዜ ቆይታ ቦኋላ ውይይቱ መደረጉን ጠቅሰው በውይይቱ ወቅት የተነሱ ነጥቦች ማለትም የሥራ ሰዓት አከባበር፣ ለታካሚ በተሳለጠ ሁኔታ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር፣ መዲሀኒቶችን በአግባቡ አገልግሎት ላይ ከማዋል አንጻር እንዲሁም የሆስፒታሉ የጽዳት ሁኔታ ለታካሚዉ እንደ ተግዳሮት በማንሳት ሰራተኞቹም የተነሱት ነጥቦች ትክክል እንደሆነና በነጥቦቹ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል።
በተመሳሳይ መልኩ የበጎ አድራጎት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ሆስፒታሉ በክረምት ጊዜ ለ11,500 የማህበረሰብ አባላት አገልግሎት ለመስጠት አቅዶ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎቱ አፈጻጸም ከ78.6 % ላይ ማድረስ መቻሉን የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሆስፒታልና የጤና ኢንስቲትዩቱ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ሳፋይ ኤሌማ ገልፀዋል።
አክለውም ይህ የበጎ አድራጎት አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና በዚሁ ሁኔታ ከቀጠልን ከእቅዳችን በላይ መስራት እንደምንችል በመጥቀስ፣ ይህን ስራ በሀላፊነት ወስደው እየሰሩ ላሉት አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በዚሁ መሰረት ሁሉም የስራ ክፍል ሀላፊዎችም፣ የተነሱ ነጥቦችን ነቅሰዉ በመውሰድ ችግሮቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ መስተካከል እንዳለባቸዉ አቅጣጫ በማስቀመጥ የዕለቱን ውይይት አጠናቀዋል።