በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ‹‹ፍትህን ማጎልበት፤ክህሎትን ማዳበር ለፍትሃዊ እና ዉጤታማ ባህላዊ የግጭቶች አፈታት›› በሚል ርዕስ ለባህላዊ ፍርድ ቤት ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጠ፡፡
Posted by admin on Tuesday, 17 December 2024

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም (BHU)
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል ዕዉቀት ሠላምን ከማረጋገጥ አኳያ የሚያበረክተዉ አስተወጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ የገዳ እና ባህል ጥናት ኢንሲቲትዩት በመክፈት እንደ አንድ ትኩረት መስክ አድርጎ እየሠራበት ይገኛል፡፡
‹‹የገዳ ሥርዓት መከባበርን፤ትብብርንና አንድነትን የሚያስተምር የማህበራዊ አስተዳደር ሥርዓት እንደ መሆኑ መጠን በሰዎች መካከልም ግጭቶችና መቃቃሮች ሲፈጡሩ የሚፈቱበት ሥርዓቶች አሉት፡፡
ይህንኑ አስመልክቶ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት መደገፉ አስፈላጊ በመሆኑ‹‹ፍትህን ማጎልበት፤ክህሎትን ማዳበር ለፍትሃዊና ዉጤታማ ባህላዊ የግጭቶች አፈታት››በሚል ርዕስ የገዳ እና ባህል ጥናት ኢንስቲትዩት ከቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህብረሰብ አገልግሎት ጋር በመተባበር የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማን ጨምሮ የምዕራብ ጎጂ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሰኚ አየለ፤የዱግዳ ዳዋና አባያ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች፤የዞኑ ባህልና ቱርዝም ባለሙያዎች እና ከዞኑ ከተለያዩ ቀበሌዎች የተወጣጡ የባህላዊ ፍርድ ቤት ተወካዮችና ሌሎችም የሚመለከታቸዉ ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዉ ተሰጥቷል፡፡
በሥልጠናዉ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማ ዩኒቨርሲቲዉ ወሳኝ የትኩረት መስክ አድርጎ ከሚሰራባቸዉ የትምህርት ዘርፍ አንዱ የሀገር በቀል ዕዉቀት መሆኑን በመጥቀስ ይህንኑን ዕዉቀት በመቀመር ለህዝቦች አንድነትና ሠላምን ከማረጋገጥ አኳያ ሚናዉ የጎላ እንዲሆንና ለቀጣይ ትዉልድ ሳይበረዝና ሳይከለስ ለማስተላለፍ እንዲቻል የገዳ ኢንስቲትዩት በመክፈት ተማሪዎችን ተቀብሎ እስከ ሦስተኛ ድግሪ ድረስ እያስተማረ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
አያይዘዉም ፕሬዝዳንቱ ሲናገሩ በዛሬዉ ዕለት ባህላዊ የፍትህ ሥርዓትን በሚመለከት የተዘጋጀዉ የአቅም ግንባታ ሥልጠና በአካባቢዉ የሚፈጠሩ ችግሮች ካሉ በቀላሉ እንዲፈቱ ከማድረጉም ባሻገር መደበኛዉን የፍርድ ቤት ሥራ ጫናን የሚቀንስ መሆኑን አስረድቷል፡፡
የገዳ እና ባህል ጥናት ኢንሲቲትዩት ዳይሬክተር መ/ር ሶራለ ጂሎ በበኩላቸዉ የመማር ማስተማር ሂደቱን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ሀገር በቀል ዕዉቀት የታከለባቸዉ በርካታ ሥራዎች በኢንስቲትዩቱ አማካይነት እየተሠሩ መሆናቸዉን ጠቅሰዉ ይህ በዓይነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አማራጭ የፍትህ ሥርዓትን ለማጠናከር በሚል የተዘጋጀዉ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ኢንስቲትዩቱ ማህብረሰቡን ለመደገፍ ካስቀመጣቸዉ አቅጣጫዎች አንዱ ስለመሆኑ ተናግሯል፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ሥልጠናዉን በአጋርነት የሰጡት የቴክኖሎጂ ሽግግር እና ማህብረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር መ/ር ንጉሰ ጎዳና ዩኒቨርሲቲዉ የሚያከናዉናቸዉ በርካታ ተግባራት ወደ ማህብረሰቡ በማድረስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለያዩ ስልቶችን ቀይሶ እየሠራ መሆኑን በመጥቀስ በዛሬዉ ዕለት የተዘጋጀዉ የአቅም ግንባታ ሥልጠናም በአካባቢዉ ፍትህን ከማረጋገጥ አኳያ ሚናዉ የጎላ መሆኑን በማመን ለስልጠናዉ ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ሥልጠናዉን የሰጡት የገዳ እና ባህል ጥናት ኢንሲቲትዩት መ/ር እና ዕጩ ዶክተር ጌታቸዉ ታደሰና ዕጩ ዶክተር ማንዶ ዶዮ ሲሆኑ በአጠቃላይ የሥልጠናዉ አስፈላጊነት፤ፍትህን ከማረጋገጥ አንፃር ባህላዊ የፍትህ ሥርዓት ያለዉ ጠቀሜታና እንዲሁም ባህላዊ የፍትህ ሥርዓት ከገዳ ሥርዓት ጋር ያለዉን ዝምድና ጭምር በማጣቀስ ሥልጠናዉን በመስጠት አጠናቋል፡፡




















































