በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅ እየተሰጡ ባሉ የሁለተኛ ድግሪ ትምህርት ፕሮግራሞች ዙሪያ የሥርዓተ-ትምህርት ፍተሻ ዉይይት ተካሄደ፡፡
Posted by admin on Tuesday, 17 December 2024

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ህዳር 21/2017 (BHU)
በመማር ማስተማሩ ሂደት የትምህርት ጥራቱንም ሆነ ተገቢነቱን ከማረጋገጥ አኳያ ከሚተገበሩ ተግባራት አንዱ በየደረጃዉ እየተሰጡ ባሉ የትምህርት ፕሮግራሞች ላይ የሚደረግ የሥርዓተ-ትምህርት ፍተሻ አንዱ በወሳኝ ደረጃ ይታያል፡፡
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ሳይንስ ኮሌጅም በአሁኑ ሰዓት በግብርና ኮሌጁ እየተሰጡ ባሉ የሁለተኛ ድግሪ የትምህርት ፕሮግራሞች ዙሪያ የሥርዓተ-ትምህርት ፍተሻ በማድረግ የበለጠ የመማር ማስተማሩን ሂደት ዉጤታማ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ከሚመከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ዉይይት አድርጓል፡፡
በዉይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ዮሐንስ ኡርጌሳ የሥርዓተ-ትምህርት ፍተሻ ማድረጉ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አኳያ ድርሻዉ የጎላ መሆኑን ጠቅሰዉ በኮሌጁም ይህን ማድረጉ አስፈላጊና ወቅቱን የጠበቀ ስለመሆኑ ተናግሯል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ግብርና በሀገር ደረጃም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እተመራ መሆኑን የጠቀሱት የኮሌጁ ዲን በዩኒቨርሲቲያችንም ግብርና አንዱ የልህቀት ማዕከል ከመሆኑም ጋር ተያይዞ በጥሩ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ በሁለተኛ ድግሪ ደረጃ እየተሰጡ ባሉ የትምህርት ፕሮግራሞች ዙሪያ የሥርዓተ-ትምህርት ፍተሻ በማድረግ የመማር ማስተማሩን ሂደት የበለጠ ማጠናከሩ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖ የተዘጋጀ ዉይይት መድረክ መሆኑንም በንግግራቸዉ ዉስጥ አካቷል፡፡
አያይዘዉም የኮሌጁ ዲን የተዘጋጀዉ የትምህርት ፕሮግራሞች የሥርዓተ ትምህርት ፍተሻ ሙሉ በሙሉ በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ ተቀርጾ የመጣዉን ሥርዓተ ትምህርት የመቀየር ጉዳይ ሳይሆን ተቋሙ በግብርናዉ ዙሪያ አሁን በደረሰበት ዕድገት ደረጃ ልክ በሚመጥን መልኩ በኮሌጁ በሁለተኛ ድግሪ ትምህርት ዘርፍ እየተሰጡ ባሉ ስድስት የትምህርት ፕሮግራሞች ዙሪያ መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ የበለጠ የመማር ማስተማሩን ሂደት ለማሳለጥ፤የተሻሻሉና በምርምር የተደገፉ የግብርና ዉጤቶችን ለሰፊዉ ማህብረሰብ ከማዳረስ አኳያ ታስቦና ተቋሙ በግብርናዉ ዙሪያ በጥሩ መሰራት ላይ እንዲቆም ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ ስለመሆኑ ተናግሯል፡፡
የሥርኣተ ትምህርት ፍተሻ የተደረገባቸዉ የትምህርት ፕሮግራሞች Animal Production, Animal Breeding and Genetics ,Rural Development, sustainable Natural Resources Management, Agronomy እና Plant Pathology ሲሆኑ በፕሮግራሞቹ ስርዓተ-ትምህርት ፍተሻ ላይም ከዩኒቨርሲቲዉ ምሁራን በተጨማሪ ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ፤ከሀወሳ ዩኒቨርሲቲና ከዲላ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ምሁራን ሀሳባቸዉን በበየነ መረብ በማካፈል ተሳታፊ ሆነዋል፡፡




















































