የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች ለቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ካውንስል አባላት የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጡ።

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፣ ግንቦት 24፣2017 ዓ.ም (ቡሆዩ)
በሥልጠናው ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና በየደረጃው ያሉ የካውንስል አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማ በሥልጠናው ቦታ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ሥልጠናው በመንግስት ደረጃ ከተሰጠን ተልዕኮና ዓላማ አንፃር በምን ደረጃ ላይ እንዳለን ራሳችንን የምንፈትሽበትና የታዩብን ውስንነቶች ካሉም በቀጣይ አሻሽለን በተሟላ ሁኔታ መፈፀም እንዲንችል አቅጣጫ የሚያሳየን ሥልጠና ነው በማለት የገለፁ ሲሆን ይህንኑ በሚመለከት ሥልጠናውን ለመስጠት በዩኒቨርሲቲው የተገኙትን የትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎችን አመስግኗል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናው በዋናነት በሦስት ርዕሰ ጉዳዮች ማለትም በአሁኑ ሰዓት ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች ከተሰጣቸው ተልዕኮች አንፃር የምደባና ልየታ ሁኔታ፣የዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝነት ሂደት እና ሀገራዊ አንድምታ እና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችን ከመስራት አኳያ ሥልጠናው ተሰጥቷል።
በአሁኑ ሰዓት ያሉትን የዩኒቨርሲዎች በየዘርፉ የተደረገውን ምደባና ልየታውን በሚመለከት ሥልጠናውን የሠጡት የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያ ዕጩ ዶ/ር ሰይድ መሃሙድ የተዘጋጀውን ሥልጠና ማኑዋል መነሻ በማድረግ ዩኒቨርሲቲውን በየዘርፉ የመመደብና የመለየት አስፈላጊነቱና ጠቀሜታው፣በየዘርፉ የተለዩት ዩኒቨርሲቲዎች ተልዕኮና ዓላማ እንዲሁም ፍኖተ ካርታን በሚመለከት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሬሄንስቭ ዩኒቨርሲቲ እንደ መሆኑ መጠን ከሌሎች በተለዬ መልኩ ትኩረት ተደርጎ መሠራት ባለባቸው ተግባራት ዙሪያ ገለፃ አድርጓል።
በዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝነት ሂደትና ሀገራዊ አንድምታው በሚለው ርዕስ የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ጌትነት ታምራት ሥልጠና የሰጡ ሲሆን የራስ ገዝነት ተግዳሮቶችና የወደፊት አቅጣጫዎች፣ከመንግስት ተቋምነት ቀስ በቀስ ስለ መላቀቅ፣ራስ ገዝ ለመሆን መሟላት ያለባቸው ጉዳዮችና የተለያዩ አለም አቀፍ ሥራዎች፣ወደ ራስ ገዝነት የሚያመሩ ስትራቴጅዎች እና አራት ዋና ዋና ምሰሶዎች፣ከመጀመሪያ ደረጃ ራስ ገዝነት እስከ ሙሉ ራስ ገዝነት ድረስ ባሉ ሂደቶች ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት እንዲሁም ሥልጣንና ተግባራት ዙሪያ ጥልቅ ማብራሪያና ገለፃ ያደረጉ ሲሆን የመማር ማስተማር ተግባር፣ የምርምር ሥራ፣ የተማሪዎች አገልግሎትና የተመራቂዎች መዳረሻ 80% እርካታ መኖር ለራስ ገዝነት ሰፊውን ቦታ እንደሚይዙ በሥልጠናው ተዳሰዋል።
አያይዘውም አቶ ታምራት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ራስ ገዝነትን አስመልክቶ አዋጅ ወጥቶና ጸድቆ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተግባራዊ መሆን የጀመረ መሆኑን የገለፁ ሲሆን በቀጣይ ሁለት አመታትም ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ራስ ገዝነት እንደሚመጡም አስረድቷል።
በተጨማሪም ዕጩ ዶ/ር ሰይድ መሃመድ የሥልጠናው መጨረሻ ርዕስ በሆነው ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የምርምር ሥራዎችን ከመሥራት አኳያ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና የሰጡ ሲሆን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃ የሚመጡ የፖሊስ ግብዓቶች ምክረ ሀሳቦች በመንግስት ደረጃ ያላቸው ተቀባይነትና አስፈላጊነት ዙሪያ፣ የፖሊስ ግብዓት አስፈላጊነትና አላማ ፣ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሥራዎች ሰነድ አዘገጃጀት ፣የሰነዱ ስታዳርድ እና ማካተት ያለባቸው ዋናና ዝርዝር ተግባራት ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ለተለያዩ ፖሊሲዎች ግብዓት የሚሆኑ ምርምር ሥራዎችን መሥራትና ምክረ ሀሳቦችን ማቅረብ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚጠበቁ ተቀዳሚ ተግባራት መካከል አንዱ ስለ መሆኑ የገለፁ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝነት ጋር ተያይዞም አንዱ መመዘኛ መስፌርት ስለ መሆኑ አንስቷል።
በመጨረሻም ተሣታፊዎቹ ከተሰጣቸው ሥልጥና በርካታ ቁምነገሮችን እንደ ጨበጡ ያነሱ ሲሆን ፣ ለተጨማሪ ግንዛቤ በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያም በአሠልጣኞችና በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ብርሃኑ ለማ በኩል ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶ ቀጣይ የሥራና የግንኙነት አቅጣጫም ተቀምጧል።