በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ “ባህላዊ ህክምና እና ሀገር በቀል የህክምና ልምዶች ከዘመናዊ ጤና አጠባበቅ ሥርዓት አንፃር፡ ከማወቅ እስከ ትብብር” በሚል መሪ ቃል ዎርክሾፕ ተካሄደ፡፡

ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ፣ ህዳር 01/2018 ዓ.ም (ቡሆዩ)
በሀገር በቀል ህክምና ዕዉቀት ዙሪያ በተናጠል የሚሠሩ ሥራዎችን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በአንድ ላይ በማገናኘት በዘርፉ የተሻለ ሥራ ለመሥራትና የተመራማሪዎችን አቅም ለመገንባት ታሳቢ ያደረገ ዎርክሾፕ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ከጤና ሚኒስቴር፤ከተለያዩ ወረዳዎች የተጋበዙ የባህልና ቱሪዝም የሥራ ኃላፊዎች እና ከተለያዩ አካባቢዎች የተጋበዙ የባህል ህክምና አዋቂዎች በተገኙበት ዎርክሾፕ ተካሂዷል፡፡
በዎርክሾፑ ላይ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አብነት በቀለ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ ሀገር በቀል ዕዉቀቶች ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ አንፃር በአሁኑ ጊዜ በተባበሩት መንግስታት ዘላቂ ግቦች ዉስጥ አንዱ መሆኑን የገለፁ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያም ለሀገር በቀል ዕዉቀቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት በትምህርት ሥርዓቱ ዉስጥ ለማካተት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደ ሆነ አስረድቷል፡፡
አያይዘዉም ዶ/ር አብነት በጉዳዩ ዙሪያ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲም ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተለየ መልኩ የራሱን ኢንስቲትዩት ጭምር በመክፈት በስፋት ሥራዎን እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ተሞክሮዉን ለሌሎች ለማስተላለፍም ተደጋጋሚ ኮንፈረንሶችና ዎርክሾፖች መደረጋቸዉን አስረድቷል፡፡
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ፤
ምርምር፤ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህብረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት በበኩላቸዉ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ዘመናዊ የህክምና ከመምጣቱ በፊት ማህብረሰቡ ራሱን በራሱ እያከመ የቆየበት ጥበብ ብዙም ትኩረት ሳይሰጥ የተረሳ በመሆኑ በአሁኑ ሰዓት በመንግስት ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠዉ ተግባር መሆኑን በማስረዳት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲም ይህንኑ ተከትሎ የሀገር በቀል ዕዉቀትን እንደ አንድ የልህቀት መስክ መለየቱን የገለፁ ሲሆን በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ ለማስኬድ የዛሬዉ መድረክ መድላድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዕለቱም የባህላዊ ህክምና ሥርዓት አጠቃላይ እይታ፤በዘርፉ ጤና ሚኒስቴር እየሠራባቸዉ ካሉት ሥራዎች፤ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና የተዘጋጁ የፖሊስ ማዕቀፎች ዙሪያ ጭምር ጽሑፎች ቀርበዉ ዉይይት ተደርጎበታል፡፡
የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የጀመረዉን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንዲችል የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን በዋናነት የባህል ህክምና አዋቂዎችን መረጃ ማደራጀት፤የባህል ህክምና በባህሪዉ የተለያዩ አካላትን ቅንጅት የሚጠይቅ ሥራ በመሆኑከሚመለ-
ከታቸዉ አካላት ጋር በጥምረት መሥራት፤የዩኒቨርሲቲዉ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍልና የፋርማሲ ትምህርት ክፍል ከ(AHARI) Armauer Hansen Research Institute ጋር በጥምረት እንዲሠሩና ለመድሃኒትነት የሚያገለግሉ ሀገር በቀል ዛፎች በዩኒቨርሲቲዉ አካባቢ ተተክለዉ የሚጠበቁበት (botanical garden) `እንዲዘጋጅ ጭምር አስተያየቶች ተሰጥቶበታል፡፡















































